+251115581070
  • Appointment
ለጥንቃቄ እዳን መልሶ ማዋቀርን በተመለከተ በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ

ለጥንቃቄ እዳን መልሶ ማዋቀርን በተመለከተ በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ

በጥቂቱ ዝርዝር ተግባራት ልዩ ሁኔታዎች
በአዋጅ ቁጥር 1243/2013 አንቀጽ 588(2) ላይ እንደተመለከተው ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓት የሚከፈተበት ሌሎች የሚመለከታቸው ገንዘብ ጠያቂዎች በሙሉ ድምጽ የሚፈቅዱ ከሆነ፤ በባለዕዳው ላይ እንደአሁን ባለ ወቅት የገጠመውን የፋይናንስ ችግር  በተከሰቱ ያልታሰቡ ኹነቶች ምክንያት ተስፋ የሚጣልባቸው ተበዳሪዎች ውልን መሰረት ባደረገ መልኩ በጊዜ ዕዳቸውን ቀልጣፋ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ መልሰው እንዲያዋቅሩ እና ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ወይም የንግድ ሥራ እንቅስቃሴው በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ የንግድ ሥራ ለመሸጥ መዘጋጀት እንዲችሉ በማድረግ አሁናዊ የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን ረተው እንዲወጡ ማስቻል ነው።
ለአፈጻጸም ይረዳም ዘነድ የተዋናይ ሚናን በመለየት ዝርዝር ተግራባራቸውን መግለጹ ለሂደቱና ለፍትህ ስራዓቱ ብሎም ለንግድ ማኅበረሰቡ የራሱ የሆነ አስተዋጽዖ ይኖረዋል በሚል በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የሐበሻ የጥብቅና አገልግሎት ኃ.የተ.የሽ.ማኅበር ይህንን ጽሑፍ አቅርቧል። መልካም ንባብ።


1.    የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

1.1.    ክፍያ

1.2.    በጊዜ ረገድ

2.    የሥነ ስርዓቱ ተጠቃሚ / ባለዕዳ

3.    ለጥንቃቄ እዳን የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያ/ዎች/

3.1.    ግዴታዎች

3.2.    ሥልጣን፡

4.    ባለገንዘብ/ቦች/

5.    ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅድ

6.    በዕቅዱ ሊካተቱ የሚችሉ

7.    የእቅዱ መጽደቅ


    የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

•    ለጥንቃቄ እዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ስርዓትን ለመክፈት ስልጣን የተሰጠው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በን.ሕ.ቁ 600 ላይ ተመልክቷል። እንዲሁም በን.ሕ.ቁ 602(2) መሰረት ለቅድመ ጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓት፣ እንዲከፈት የሚሰጥ ፍርድ ዓለም አቀፋዊ ተፈጻሚነት አለው።
•    በን.ሕ.591 (2) የክፍያ መቋረጥ ጋር በተገናኘ ፍርድ ቤቱ በራሱ ወይም በሌላ በተመለከቱ አካላት አቤቱታ ሲቀርብለት ውሳኔ የባለዕዳውን ጉዳዮች እና እንቅስቃሴዎች የሚመረምር መርማሪ ሊሾም ይችላል፤
•    ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓትን የከፈተው ፍርድ ቤት ከእነዚህ ሥነ ሥርዓቶች በቀጥታ በሚመነጩ እና ከእነሱ ጋር በቅርበት በሚገናኙ የሚከተሉትን ጉዳዮች እንደሚመለከቱት ባሉ ክሶች ላይ ሥልጣን አለው፡-
ሀ) መልሶ የማዋቀር እና መልሶ የማደራጀት ዕቅድ፣
ለ) በንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያለን ድርጅት በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ እንዲሸጥ ማጽደቅ፣
ሐ) በሂደት ላይ ያሉ ውሎች፣
መ) የተቆጣጣሪ ዳኛዎች፣ የባለዕዳው ንብረት ጠባቂዎች፣ ተቆጣጣሪዎች እና ዳይሬክተሮች ኃላፊነት፣
ሠ) የክፍያ ጥያቄዎች አቀራረብ፣ ማረጋገጥ እና አቀባበል፣
ረ) ከንብረት የሚመነጩ መብቶች፣
ሰ) ማቻቻል
ሸ) የንብረቶች መሸጥ ወይም መተላለፍ፣
ቀ) የክፍያ ጥያቄዎች ቅደም ተከተል፣
በ) ከሽያጭ የተገኘ ገንዘብ ክፍፍል፣
ተ) የድርጊቶች ፈራሽ መደረግ፣
ቸ) ውሎችን ማጽናት እና ተፈጻሚነት፣
ኀ) የባለዕዳው ነጻ መውጣት፣
ነ) የሥነ ሥርዓቱ መዘጋት።
•    በን.ሕ.ቁ 619 መሰረት ለጥንቃቄ እዳን መልሶ ማዋቀር ባለሞያ ለመሾም ስልጣን የተሰጠው ሲሆን በአንቀጽ 620 መሰረት በባለገንዘቦች ጥያቄ እና በ2/3ኛ ባለገንዘቦች ድጋፍ ሌላ ሞያተኛ ለመተካት ስልጣን ተሰጥቶታል።

1.1.    ክፍያ
•    ለሚሾሙት ለጥንቃቄ እዳን የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያዎች ክፍያ በባለዕዳዋ/ው እና በዘርፉ ባለሞያዎች መካከል በሚደረግ ንግግር የሚወሰን ሲሆን ዋጋው መጠን በፍርድ ቤት መጽደቅ አለበት።
1.2.    በጊዜ ረገድ
•    በአንቀጽ 618 መሰረት የሥነ ሥርዓቱ የቆይታ ጊዜ አስመልክቶ በንዑስ አንቀጽ 1 ላይ  ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅዱ ከሚመለከታቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ጋር በአራት ወራት ውስጥ መጠናቀቅ ይኖርበታል፤
•    በዚህ ጊዜ ያላለቀ እንደሆነም ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ እንደሚችል እና ይህ ጊዜ ከ8 ወር ሊበልጥ አይችልም።

2.    የሥነ ስርዓቱ ተጠቃሚ / ባለዕዳ
•    ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅድ ማዘጋጀት፣ በሂደቱ ከጥንቃቄ እዳን ማዋቀር ባለሞያዎችን ድጋፍ መጠየቅ እና ማግኘት (አንቀጽ 627)
•    የንግድ ስራውን በይዞታ ስራ አድርጎ መምራት እና ገደብ ከተጣለበት ስልጣን ውጭ በግል ውሳኔ መስጠት፤
•    አስቀድመው ነጠላ እገዳ ከተላለፈባቸው ዕዳዎች በስተቀር ባለዕዳው በመደበኛ የሥራ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ዕዳዎችን በሙሉ ባለዕዳዋ/ው መክፈል ይኖርባታል፤
•    መደበኛ እዳ ክፍያ ማቋረጥ ለእንደገና ማደራጀት ወይም ኪሳራ ስርዓት ይዳርጋል።/ን.ሕ.ቁ 626 እና 702/

3.    ለጥንቃቄ እዳን የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያ/ዎች/
•    ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ስርዓት እንዲከፈት በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰጠቱን ተከትሎ ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ይሾማል/ሉ።
•    በን.ሕ.ቁ  619 መሰረት መሰረት ማንኛውም ገንዘብ ጠያቂ ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያው እንዲተካ አቤቱታ ሊያቀርብ ይችላል፤
•    በን.ሕ.ቁ 592(2) የሚሾም መርማሪ ቢኖር ሹመኛውን የማገዝ ግዴታ አለበት።

•    በን.ሕ.ቁ 599 መሰረት መረጃ ለባለገንዘቦች በጽሁፍ ሲጠየቁ ለጥያቄው አጥጋቢ ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለባቸው። ሆኖም ጥያቄ ምክንያታዊ ካልሆነ ወይም ከመጠን በላይ ጫና የሚያሳድር ከሆነ ብቻ ያለመቀበል ስልጣን አላቸው።
•    ከታች ያሉ ዝርዝር ግዴታዎች በን.ሕ.ቁ 621 ላይ ተመልክተዋል
3.1.    ግዴታዎች
•    ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያው ራሱን ችሎ በመንሳቀስ የሚከተሉትን እንዲሁም ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል፡-
ሀ) ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ በማዋቀር ሥነ ሥርዓቱ ውስጥ የሚሳተፉትን ገንዘብ ጠያቂዎች መወሰን፣
ለ) መልሶ የማዋቀር ዕቅድ በማርቀቅ እና በመደራደር ረገድ ባለዕዳውን እና ገንዘብ ጠያቂዎቹን ማገዝ፣
ሐ) የገንዘብ ጠያቂዎቹን ስብሰባዎች መጥራት እና በሊቀ መንበርነት መምራት፣
መ) ዕዳን መልሶ በማዋቀር ዕቅድ ላይ ድርድር በሚደረግበት ወቅት የባለዕዳውን እንቅስቃሴዎች መቆጣጠር እና ድርድሩ የሚገኝበትን ደረጃ በተመለከተ በየጊዜው ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት ማቅረብ፣
ሠ) ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅዱን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ማስጸደቅ፣ እና
ረ) እንደሁኔታው በንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያለን ድርጅት በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ እንዲሸጥ ማዘጋጀት፤
3.2.    ሥልጣን፡
•    የባለዕዳዋ/ውን መሰረታዊ የሆኑ ንብረቶች ሽያጭና ግዥ ማጽደቅ /ን.ሕ.ቁ 624 አብዛኛውን ንብረት እንደመሸጥ እና የዋስትና መብት እንደመፍጠር ያሉ ከመደበኛ የሥራ ሂደት ውጭ የሆኑ ማናቸውም ውሳኔዎች ዕዳን መልሶ በማዋቀር ዘርፍ ባለሞያው አስቀድመው መጽደቅ እንዳለባቸው ተመልክቷል/
ሀ) ባለዕዳው ወይም ማንኛውም ሦስተኛ ወገን ማንኛውንም አስፈላጊ የሆነ ተጨማሪ የገንዘብ ወይም የሒሳብ መረጃ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠት፣
ለ) የባለዕዳውን የገንዘብ ሁኔታ እና የንግድ ሥራ ዕቅድ ኦዲት እንዲያደርጉ ጭምር ገለልተኛ ባለሞያዎችን መሾም።

4.    ባለገንዘብ/ቦች/
•    አንቀጽ 597 መሰረት ይህ ስነስርዓት አጠቃላይ መርህ የገንዘብ ጠያቂዎችን ትክክለኛ ጥቅም ማስጠበቅ ነው፤ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ በማዋቀር ሥነ ሥርዓት ውስጥ መልሶ የማዋቀር ዕቅዱ በሁሉም በሚመለከታቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ሙሉ ድምጽ መጽደቅ እንዳለበት ከመደንገጉ በላይ በአንቀጽ 627(1) መሰረት በባለዕዳዋ/ው የተዘጋጀው ለጥንቃቄ እዳን መልሶ ማዋቀር ዕቅዱን ለማሻሻል ጥያቄ የማቅረብ እና የአጸፋ-ሀሳብ የማቅረብ መብት አላቸው፤
•    አንቀጽ 598 የገንዘብ ጠያቂዎች ተሳትፎ ገንዘብ ጠያቂዎች በሥነ ሥርዓቶች ወቅት በአጠቃላይ አስተያየታቸውን የማቅረብ እና ፍርድ ቤት ጉዳዮችን በሚሰማበት ጊዜ የመሰማት መብት አላቸው።
•    በን.ሕ.ቁ 599 መሰረት መረጃ የመጠየቅና የማግኘት መብት አላቸው።

5.    ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅድ
•    በባለእዳዋ ይዘጋጃል፤
•    ለጥንቃቄ ዕዳን የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያዎች እቅዱ ዝግጅት ላይ ለባለዕዳዋ/ው ድጋፍ ይደረጋል፤
•    በባለገንዘቦች በተናጥል ወይም በጉባዔያቸው በእቅዱ ላይ ሃሳብ የማቅረብ እና እንዲሻሻል የአጻፋ ሃሳብ ማቅረብ መብት አላቸው፤
•    ዕቅዱ ላይ ተሳታፊ ባለገንዘቦች የተቃውሞ እና የድጋፍ ድምጽ የመስጠት መብት አላቸው፤
•    ለጥንቃቄ እዳን መልሶ ማዋቀር ስነ ስርዓቱ ከባለገንዘቦች ጋር በተጀመረ በ4 ወራት መጠናቀቅ አለበት። በዚህ ጊዜ ያላለቀ እንደሆነም ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ እንደሚችል እና ይህም ጊዜ ከ8 ወር ሊበልጥ አይችልም።
•    ዕዳን መልሶ የማዋቀር ዕቅዱ ዕዳን መልሶ በማዋቀር ሥነ ሥርዓቱ ውስጥ በሚሳተፉ የሚመለከታቸው ገንዘብ ጠያቂዎች በሙሉ ተቀባይነት ማግኘት አለበት፤

6.    በዕቅዱ ሊካተቱ የሚችሉ
ሀ) ለሚመለከታቸው ገንዘብ ጠያቂዎች የክፍያ ጥያቄዎች እንደገና የጊዜ ሰንጠረዥ ማውጣት፣ /rescheduling of the claims/
ለ) የሚመለከታቸው ገንዘብ ጠያቂዎችን የክፍያ ጥያቄዎችን መተው፣/waiver of claims/
ሐ) የገንዘብ ዕዳ ሰነዶችን አወጣጥ በሚመለከቱ ሕጎች መሰረት የገንዘብ ዕዳ ሰነዶችን በማውጣት የክፍያ ጥያቄዎችን መፍታት፣ /issuing of financial debt instruments/
መ) የሚመለከታቸውን ገንዘብ ጠያቂዎች የክፍያ ጥያቄዎች ወደ አክሲዮን መቀየር፣
ሠ) የዚህ ሕግ አስገዳጅ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በገንዘብ ጠያቂው ወይም በሦስተኛ ወገን ኢንቨስተሮች የሚገዛውን የባለዕዳውን ካፒታል መጠን መቀነስ ወይም መጨመር፣
ሸ) ለገንዘብ ጠያቂው ወይም ለሦስተኛ ወገን ኢንቨስተሮች ነባር አክሲዮኖችን መሸጥ ወይም አዲስ አክሲዮኖችን ማውጣት።
ቀ) እዳን አከፋፈልን ለማረቅ የሚያስችል አዲስ ገንዘብ ምንጭ ማግኘት

7.    የእቅዱ መጽደቅ
•    እቅዱ በባለዕዳዋ/ው ተዘጋጅቶ፣ በተስታፊ ባለገንዘቦች ተቀባይነት ያገኘ እንደሆነ ለጥንቃቄ እዳን የማዋቀር ዘርፍ ባለሞያ/ዎች/ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ በማድረግ እንዲጸድቅ ይሆናል።
•    ይህ እቅድ በፍርድ ቤቱ ከጸደቀ በኋላ ተፈጻሚ እንደሚሆን በን.ሕ.ቁ 629 ላይ ተመልክቷል።

Share This

Comments