የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነዉን የጥብቅና ድርጅት (Law Firm) ፈቃድ ሰጠ




Date: 2022-04-07

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግስት የሕግ አገልግሎት ዘርፍን ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አዲስ የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 ማዉጧቱ የታወሳል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማህበር መመስረቱና አመራሮች በጠበቆች ጠቅላላ ጉባኤ ተመርጠዉ ሥራ መጀመራቸዉ ይታወቃል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴርም ከአዲሱ የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማህበር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አዋጁን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር የአሰራር መመሪያዎችና ዉስጠ ደንብ መቅረጽን ጨምሮ አደራጃጀቶችን በመፍጠርና መነሻ የሚሆን የሰዉ ሃይል እና ግብዓት በመመደብ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲሱ የጠበቆች አዋጅ አንቀጽ 37 መሰረት የፀና የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው ቢያንስ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ጠበቆች አንድ ላይ በመሆን የጥብቅና ድርጅት ማቋቋም እንደሚችሉ የተደነገገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር መስፈርቱን ለሚያሟሉ አመልካቾች የጥብቅና ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት የጀመረ ሲሆን በትናንትናዉ ዕለት የመጀመሪያዉን የጥብቅና ድርጅት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዓለምአንተ አግደዉ ፈቃዱን በሰጡበት ወቅት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የጥብቅና አገልግሎት በድርጅት መስጠት የሚያስችል ሕግ መዉጣቱና ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ለዜጎች የተሻለና ጥራት ያለዉ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለዉና በደንበኞችና ጠበቆች መካከል ሊኖር የሚገባዉን መተማመን የሚያጎለበት ከመሆኑም ባሻገር የተሻለ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአዋጁ ላይ በተመለከተዉ መሰረት የጥብቅና ድርጅት ለመመስረት ወይም የሽርክና ማህበር ለማቋቋም የሚቀርብ ጥያቄ የሚመለከቱትን ዝርዝሮች መያዝ እንዳለበት ለማሳታወስ እንወዳለን፡-
1. ማህበሩን ለመመስረት በተስማሙ አባላት የተፈረመ የፈቃድ ይሰጠኝ ማመልከቻ፣
2. ከማመልከቻው ጋር በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የተረጋገጠና በሁሉም አባላት የተፈረመ የመመስረቻ ጽሁፍ፣
3. የጥብቅና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር በሚል ስያሜ የጥብቅና ድርጅት ለማቋቋም በአባላት የተፈረመ ቃለ ጉባዔ፣
4. በአባላት የተፈረመ የሸሪኮች የሽርክና ስምምነት፣
5. አመልከቾች ጠበቆች ስለመሆናቸዉ እና የታደሰ የጥብቅና ፍቃድ ያላቸው መሆናቸውን የሚገልጽ ፈቃድ ኮፒ፣
6. ማህበሩ የመድህን ዋስትና ስለመግባቱ የሚያረጋግጥ የመድህን ዋስትና ሰነድ በማያያዝ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ አመልካቾች የመመስረቻ ጽሁፋቸው በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በኩል ከመረጋገጡ በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድ አስተዳደርና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በኩል የመመስረቻ ጽሁፉ የአዋጅ ቁጥር 1249/2013 እና የንግድ ሕጉ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ላይ የተመለከቱትን መመዘኛዎች የሚያሟሉ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም አመልካቾች በሰየሙት የጥብቅና ድርጅት ስም የተመዘገበ ሌላ የጥብቅና ድርጅት የሌለ ስለመሆኑ የማረጋገጥ ሥራ ይሰራል፡፡ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዉ ሲገኝ ለኢንሹራንስ ሰጭዎችና ለሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ የትብብር ደብዳቤ በፍትህ ሚኒስቴር ከተጻፈ በኋላ ሁሉም መመዘኛዎች መሟላታቸዉ ሲረጋገጥ የጥብቅና ድርጅት ሰርተፊኬት የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ማስታወሻ፡- የፈቃድ ይሰጠኝ ማመልከቻው በቀጥታ ባምቢስ በሚገኘው የፍትሕ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ 2ኛ ፎቅ ለጠበቆች ፍቃድ አስተዳደርና ነጻ የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ይቀርባል፡፡

Leave a comment